ኦሪት ዘፍጥረት 14

1፤ በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፥ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፥ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር፥ በአሕዛብ ንጉሥ በቲድዓል ዘመን እንዲህ ሆነ፤

2፤ ከሰዶም ንጉሥ ከባላ፥ ከገሞራ ንጉሥ ከብርሳ፥ ከአዳማ ንጉሥ ከሰነአብ፥ ከሰቦይም ንጉሥ ከሰሜበር፥ ዞዓር ከተባለች ከቤላ ንጉሥም ጋር ሰልፍ አደረጉ።

3፤ እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ ተሰብስበው ተባበሩ፤ ይኸውም የጨው ባሕር ነው።

4፤ አሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎምር ተገዝተው ነበር፥ በአሥራ ሦስተኛውም ዓመት ዐመፁ።

5፤ በአሥራ አራተኛውም ዓመት ኮሎዶጎምርና ከእርሱ ጋር የነበሩት ነገሥታት መጡ፤ ራፋይምን በአስጣሮት ቃርናይም፥ ዙዚምንም በሃም፥ ኤሚምንም በሴዊ ቂርያታይም መቱ፤

6፤ የሖር ሰዎችንም በሴይር ተራራቸው በበረሀ አጠገብ እስካለች እስከ ኤል ፋራን ድረስ መቱ።

7፤ ተመልሰውም ቃዴስ ወደ ተባለች ወደ ዓይንሚስፓጥ መጡ፤ የአማሌቅን አገር ሁሉና ደግሞ በሐሴሶን ታማር የነበረውን አሞራውያንን መቱ።

8፤ የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥ፥ የአዳማ ንጉሥና የሰቦይም ንጉሥ፥ ዞዓር የተባለች የቤላ ንጉሥም ወጡ፤ እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ በእነርሱ ላይ ለሰልፍ ወጡ፤

9፤ የኤላምን ንጉሥ ኮሎዶጎምርን፥ የአሕዛብን ንጉሥ ቲድዓልን፥ የሰናዖርን ንጉሥ አምራፌልን፥ የእላሳርን ንጉሥ አርዮክን ለመውጋት አምስቱ ነገሥታት በእነዚህ በአራቱ ላይ ወጡ።

10፤ በሲዲም ሸለቆ ግን የዝፍት ጕድጓዶች ነበሩበት። የሰዶም ንጉሥ የገሞራ ንጉሥም ሸሹና ወደዚያ ወደቁ፤ የቀሩትም ወደ ተራራ ሸሹ።

11፤ የሰዶምንና የገሞራን ከብት ሁሉ መብላቸውንም ሁሉ ወስደው ሄዱ።

12፤ በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን ደግሞ ከብቱንም ወስደው ሄዱ።

13፤ አንድ የሸሸ ሰውም መጣ፥ ለዕብራዊው ለአብራምም ነገረው፤ እርሱም የኤስኮል ወንድምና የአውናን ወንድም በሆነ በአሞራዊ መምሬ የአድባር ዛፍ ይኖር ነበር፤ እነዚያም ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር።

14፤ አብራምም ወንድሙ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ የተወለዱትን ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ብላቴኖቹን አሰለፈ፥ ፍለጋቸውንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ።

15፤ ብላቴኖቹንም ከፍሎ በሌሊት እርሱ ከባሪያዎቹ ጋር ወረደባቸው፥ መታቸውም፥ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው።

16፤ ከብቱንም ሁሉ አስመለሰ፥ ደግሞም ወንድሙን ሎጥንና ከብቶቹን ሴቶችንና ሕዝቡን ደግሞ መለሰ።

17፤ ኮሎዶጎምርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመለሰ በኋላም የሰዶም ንጉሥ የንጉሥ ሸለቆ በሆነ በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ።

18፤ የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ።

19፤ ባረከውም። አብራም ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤

20፤ ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም የተባረከ ነው አለውም። አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው።

21፤ የሰዶም ንጉሥም አብራምን። ሰዎቹን ስጠኝ፥ ከብቱን ግን ለአንተ ውሰድ አለው።

22፤ አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው። ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፤

23፤

24፤ አንተ። አብራምን ባለጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ ብላቴኖቹ ከበሉት በቀር ከእኔ ጋር ከሄዱትም ድርሻ በቀር፥ ፈትልም ቢሆን የጫማ ማዘቢያም ቢሆን፥ ለአንተ ከሆነው ሁሉ እንዳልወስድ፤ አውናን ኤስኮልም መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ። a