ኦሪት ዘፍጥረት 16

1፤ የአብራም ሚስት ሦራ ግን ለአብራም ልጅ አልወለደችለትም ነበር፤ ስምዋ አጋር የተባለ ግብፃዊት ባሪያም ነበረቻት።

2፤ ሦራም አብራምን። እነሆ፥ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ፤ ምናልባት ከእርስዋ በልጅ እታነጽ እንደ ሆነ ወደ እርስዋ ግባ አለችው።

3፤ አብራምም የሦራን ቃል ሰማ። አብራምም በከነዓን ምድር አሥር ዓመት ከተቀመጠ በኋላ፥ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት ባሪያዋን አጋርን ወስዳ ለባልዋ ለአብራም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው።

4፤ እርሱም ወደ አጋር ገባ፥ አረገዘችም፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እመቤትዋን በዓይንዋ አቃለለች።

5፤ ሦራም አብራምን። መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይንዋ አቃለለችኝ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ አለችው።

6፤ አብራምም ሦራን። እነሆ ባሪያሽ በእጅሽ ናት፤ እንደ ወደድሽ አድርጊባት አላት። ሦራም ባሠቀየቻት ጊዜ አጋር ከፊትዋ ኮበለለች።

7፤ የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በበረሀ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በምትወስደው መንገድ አጠገብ ነው።

8፤ እርሱም። የሦራ ባሪያ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ? አላት። እርስዋም። እኔ ከእመቤቴ ከሦራ የኮበለልሁ ነኝ አለች።

9፤ የእግዚአብሔር መልአክም። ወደ እመቤትሽ ተመለሺ፥ ከእጅዋም በታች ሆነሽ ተገዥ አላት።

10፤ የእግዚአብሔር መልአክም። ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፥ ከብዛቱም የተነሣ አይቆጠርም አላት።

11፤ የእግዚአብሔር መልአክም አላት። እነሆ አንቺ ፀንሰሻል፥ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም እስማኤል ብለሽ ትጠሪዋለሽ፥ እግዚአብሔር መቸገርሽን ሰምቶአልና።

12፤ እርሱም የበዳ አህያን የሚመስል ሰው ይሆናል፤ እጁ በሁሉ ላይ ይሆናል፥ የሁሉም እጅ ደግሞ በእርሱ ላይ ይሆናል፤ እርሱም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ይኖራል።

13፤ እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች፤ የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና።

14፤ ስለዚህም የዚያ ጕድጓድ ስም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ ተጠራ፤ እርሱም በቃዴስና በባሬድ መካከል ነው።

15፤ አጋርም ለአብራም ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ አብራምም አጋር የወለደችለትን የልጁን ስም እስማኤል ብሎ ጠራው።

16፤ አጋር እስማኤልን ለአብራም በወለደችለት ጊዜ አብራም የሰማንያ ስድስት ዓመት ሰው ነበረ። a