ኦሪት ዘፍጥረት 32

1፤ ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፥ የእግዚአብሔር መላእክትም ተገናኙት።

2፤ ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ። እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው አለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም መሃናይም ብሎ ጠራው።

3፤ ያዕቆብም ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ወደ ሴይር ምድር ወደ ኤዶም አገር ከፊቱ መልእክተኞችን ላከ፤

4፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። ለጌታዬ ለዔሳው። ባሪያህ ያዕቆብ እንዲህ አለ ብላችሁ ንገሩት። በላባ ዘንድ በስደት ተቀመጥሁ፤ እስከ አሁን ድረስ ቆየሁ፤

5፤ ላሞችንም አህዮችንም በጎችን ወንዶች ባሪያዎችንም ሴቶች ባሪያዎችንም አገኘሁ፤ አሁንም በፊትህ ሞገስን አገኝ ዘንድ ለጌታዬ ለማስታወቅ ላክሁ።

6፤ መልእክተኞቹም ወደ ያዕቆብ ተመልሰው እንዲህ አሉት። ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ደግሞ ሊቀበልህ ይመጣል፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች አሉ።

7፤ ያዕቆብም እጅግ ፈርቶ ተጨነቀ፤ ከእርሱም ጋር ያሉትን ሰዎች መንጎችንም ላሞችንም ግመሎችንም በሁለት ወገን ከፈላቸው፤

8፤ እንዲህም አለ። ዔሳው መጥቶ አንዱን ወገን የመታ እንደ ሆነ የቀረው ወገን ያመልጣል።

9፤ ያዕቆብም አለ። የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴም የይስሐቅ አምላክ ሆይ። ወደ ምድርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፥ በጎነትንም አደርግልሃለሁ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፤

10፤ ለባሪያህ ከሠራኸው ከምሕረትህና ከእውነትህም ሁሉ ትንሽ ስንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበርና፥ አሁን ግን የሁለት ክፍል ሠራዊት ሆንሁ።

11፤ ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፤ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፥ እናቶችንም ከልጆች ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና።

12፤ አንተም። በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፥ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ ብለህ ነበር።

13፤ በዚያችም ሌሊት ከዚያው አደረ። ከያዘውም ሁሉ ለወንድሙ ለዔሳው እጅ መንሻን አወጣ፤

14፤ ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችንና ሀያ የፍየል አውራዎችን፥ ሁለት መቶ እንስት በጎችንና ሀያ የበግ አውራዎችን፥

15፤ ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎችን ከግልገሎቻቸው ጋር፥ አርባ ላም፥ አሥር በሬ፥ ሀያ እንስት አህያ፥ አሥርም የእህያ ግልገሎችን።

16፤ መንጎቹን በየወገኑ ከፍሎ በባሪያዎቹ እጅ አደረጋቸው፤ ባሪያዎቹንም። በፊቴ እለፉ መንጋውንና መንጋውንም አራርቁት አለ።

17፤ የፊተኛውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው። ወንድሜ ዔሳው ያገኘህ እንደሆነ። አንተ የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? በፊትህ ያለው ይህስ የማን ነው? ብሎ የጠየቀህም እንደ ሆነ፥

18፤ በዚያን ጊዜ አንተ። ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደደው የባሪያህ የያዕቆብ ነው፤ እርሱም ደግሞ እነሆ ከኋላችን ነው በለው።

19፤ እንዲሁም ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ከመንጎችም በኋላ የሚሄዱትን ሁሉ እንዲሁ ብሎ አዘዘ። ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት፤

20፤ እንዲህም በሉት። እነሆ ባሪያህ ያዕቆብ ከኋላችን ነው። በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይራራልኛል ፊቱንም አያለሁ ብሎአልና።

21፤ እጅ መንሻው ከእርሱ ቀድሞ አለፈ፤ እርሱ ግን በዚያች ሌሊት በሰፈር አደረ።

22፤ በዚያች ሌሊትም ተነሣ፥ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ባሪያዎቹን አሥራ አንዱንም ልጆቹን ወስዶ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ።

23፤ ወሰዳቸውም ወንዙንም አሻገራቸው፥ ከብቱንም ሁሉ አሻገረ።

24፤ ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ይታገለው ነበር።

25፤ እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ ያዕቆብም የጭኑ ሹልዳ ሲታገለው ደነዘዘ።

26፤ እንዲህም አለው። ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ። እርሱም። ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም አለው።

27፤ እንዲህም አለው። ስምህ ማን ነው? እርሱም። ያዕቆብ ነኝ አለው።

28፤ አለውም። ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና።

29፤ ያዕቆብም። ስምህን ንገረኝ ብሎ ጠየቀው። እርሱም። ስሜን ለምን ትጠይቃለህ? አለው። በዚያም ስፍራ ባረከው።

30፤ ያዕቆብም። እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች ሲል የዚያን ቦታ ስም Dኒኤል ብሎ ጠራው።

31፤ Dኒኤልንም ሲያልፍ ፀሐይ ወጣችበት፥ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር።

32፤ ስለዚህም የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ የወርችን ሹልዳ አይበሉም፤ የያዕቆብን ጭን ይዞ የወርችን ሹልዳ አደንዝዞአልና። q ቍ@

30፤ ጵኒኤል የሚለውን ቃል የግእዝ መጽሐፍ ራእየ እግዚአብሔር ይለዋል። a