ኦሪት ዘፍጥረት 40

1፤ ከዚህ ነገር በኋላም እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ የጠጅ አሳላፊና የእንጀራ አበዛ ጌታቸውን የግብፅ ንጉሥን በደሉ።

2፤ ፈርዖንም በሁለቱ ሹማምቱ በጠጅ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ አበዛዎቹ አለቃ ላይ ተቆጣ፤

3፤ ዮሴፍ ታስሮ በነበረበትም በግዞት ስፍራ በዘበኞቹ አለቃ ቤት አስጠበቃቸው።

4፤ የዘበኞቹም አለቃ ለዮሴፍ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እርሱም ያገለግላቸው ነበር፤ በግዞት ቤትም አያሌ ቀን ተቀመጡ።

5፤ በግዞት ቤት የነበሩት የግብፅ ንጉሥ ጠጅ አሳላፊና እንጀራ አበዛ ሁለቱም በአንዲት ሌሊት እንደ ሕልሙ ትርጓሜ እየራሳቸው ሕልምን አለሙ።

6፤ ዮሴፍም ማልዶ ወደ እነርሱ ገባ፥ እነሆም አዝነው አያቸው።

7፤ በጌታው ቤት ከእርሱ ጋር በግዞት የነበሩትንም የፈርዖንን ሹማምት እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው። እናንተ ዛሬ ስለ ምን አዝናችኋል?

8፤ እነርሱም። ሕልምን አልመን የሚተረጕምልን አጣን አሉት። ዮሴፍም አላቸው። ሕልምን የሚተረጕም እግዚአብሔር የሰጠው አይደለምን? እስቲ ንገሩኝ።

9፤ የጠጅ አሳላፊዎች አለቃም ለዮሴፍ ሕልሙን እንዲህ ብሎ ነገረው። በሕልሜ የወይን ዛፍ በፊቴ ሆና አየሁ፥

10፤ በዛፊቱም ሦስት አረግ አለባት፤ እርስዋም ቅጠልና አበባ አወጣች፥ ዘለላም አንጠለጠለች፥ የዘለላዋም ፍሬ በሰለ፤

11፤ የፈርዖንም ጽዋ በእጄ ነበረ፤ ፍሬውንም ወስጄ በፈርዖን ጽዋ ጨመቅሁት፥ ጽዋውንም ለፈርዖን በእጁ ሰጠሁት።

12፤ ዮሴፍም አለው። የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስቱ አረግ ሦስት ቀን ነው፤

13፤ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ ወደ ቀደመው ሹመትህም ይመልስሃል፤ ጠጅ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ስታደርግ እንደ ነበረው እንደ ቀድሞው ሥርዓትም የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ።

14፤ ነገር ግን በጎ ነገር በተደረገልህ ጊዜ እኔን አስበኝ፥ ምሕረትንም አድርግልኝ፥ የእኔንም ነገር ለፈርዖን ነግረህ ከዚህ ቤት አውጣኝ፤

15፤ እኔን ከዕብራውያን አገር ሰርቀው አምጥተውኛልና፤ ከዚህም ደግሞ በግዞት ያኖሩኝ ዘንድ ምንም አላደረግሁም።

16፤ የእንጀራ አበዛዎቹ አለቃም ሕልሙን በመልካም እንደ ተረጎመ ባየ ጊዜ ዮሴፍን እንዲህ አለው። እኔም ደግሞ ሕልም አይቼ ነበር፥ እነሆም ሦስት መሶብ ነጭ እንጀራ በራሴ ላይ ነበረ፤

17፤ በላይኛውም መሶብ ፈርዖን ከሚበላው ከጋጋሪዎች ሥራ ሁሉ ነበረበት፤ ወፎችም በራሴ ላይ ከመሶቡ ይበሉ ነበር።

18፤ ዮሴፍም መልሶ እንዲህ አለው። የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤

19፤ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ በእንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።

20፤ በሦስተኛውም ቀን ፈርዖን የተወለደበት ቀን ነበረ፥ ለሠራዊቱም ሁሉ ግብር አደረገ፤ የጠጅ አሳላፊዎቹን አለቃና የእንጀራ አበዛዎቹን አለቃ በአሽከሮቹ መካከል ከፍ አደረገ።

21፤ የጠጅ አሳለፊዎቹንም አለቃ ወደ ስፍራው መለሰው፥ ጽዋውንም በፈርዖን እጅ ሰጠ፤

22፤ የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ ሰቀለው፥ ዮሴፍ እንደተረጎመላቸው።

23፤ የጠጅ አሳላፊዎች አለቃ ግን ዮሴፍን አላሰበውም፥ ረሳው እንጂ። a