0:00

መዝሙረ ዳዊት 29

1 ከድንኳን በመውጣት ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 የአምላክ ልጆች ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አምጡ። ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ።

2 የስሙን ክብር ለእግዚአብሔር አምጡ፥ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ።

3 የእግዚአብሔር ድምፅ በውኆች ላይ፥ የክብር አምላክ አንጐደጐደ፥ እግዚአብሔር በብዙ ውኆች ላይ።

4 የእግዚአብሔር ድምፅ በኃይል ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅ በታላቅ ክብር ነው።

5 የእግዚአብር ድምፅ ዝግባን ይሰብራል፤ እግዚአብሔር የሊባኖስን ዝግባ ይቀጠቅጣል።

6 እንደ ጥጃ ሊባኖስን፥ አንድ ቀን እንዳለው አውሬ ልጅ ስርዮንን ያዘልላቸዋል።

7 የእግዚአብሔር ድምፅ የእሳቱን ነበልባል ይቈርጣል።

8 የእግዚአብሔር ድምፅ ምድረ በዳውን ያናውጣል፥ እግዚአብሔር የቃዴስን ምድረ በዳ ያናውጣል።

9 የእግዚአብሔር ድምፅ ዋላዎችን ያጠነክራቸዋል፥ ጫካዎቹንም ይገልጣል፤ ሁሉም በመቅደሱ። ምስጋና ይላል።

10 እግዚአብሔር የጥፋት ውኃን ሰብስቦአል፤ እግዚአብሔር ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይቀመጣል።

11 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይልን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል።