0:00

መዝሙረ ዳዊት 57

1 ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በዋሻ በነበረበት ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ። 1 ማረኝ፥ አቤቱ፥ ማረኝ፥ ነፍሴ አንተን ታምናለችና፤ ጉዳት እስክታልፍ ድረስ በክንፎችህ ጥላ እታመናለሁ።

2 ወደሚረዳኝ እግዚአብሔር ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጮኻለሁ።

3 ከሰማይ ልኮ አዳነኝ፥ ለረገጡኝም ውርደትን ሰጣቸው፤ እግዚአብሔር ቸርነቱንና እውነቱን ላከ።

4 ነፍሴን ከአንበሶች መካከል አዳናት። ደንግጬ ተኛሁ፤ የሰው ልጆች ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ፥ አንደበታቸው የተሳለ ሾተል ነው።

5 አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።

6 ለእግሮቼ ወጥመድን አዘጋጁ፥ ነፍሴንም አጐበጡአት፤ ጕድጓድ በፊቴ ቈፈሩ፥ በእርሱም ወደቁ።

7 ልቤ ጨካኝ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጨካኝ ነው፤ እቀኛለሁ፥ እዘምራለሁ።

8 ክብሬ ይነሣ፥ በገናና መሰንቆም ይነሡ፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ።

9 አቤቱ፥ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ በወገኖችም ዘንድ እዘምርልሃለሁ፤

10 ምሕረትህ እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ብላለችና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ።

11 አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።