ኦሪት ዘጸአት 1

1፤ ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፤ ሰው ሁሉ ከቤተ ሰቡ ጋር ገባ።

2፤ ሮቤል፥

3፤ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፥

4፤ ብንያም፥ ዳን፥ ንፍታሌም፥ ጋድ፥ አሴር።

5፤ ከያቆብ ጕልበት የወጡት ሰዎች ሁሉ ሰባ ነፍሶች ነበሩ፤ ዮሴፍም አስቀድሞ በግብፅ ነበረ።

6፤ ዮሴፍም ሞተ፥ ወንድሞቹም፥ ያም ትውልድ ሁሉ።

7፤ የእስራኤልም ልጆች አፈሩ፥ እጅግም በዙ፥ ተባዙም፥ አጅግም ጸኑ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ሞላች።

8፤ በግብፅም ዮሴፍን ያላወቀ አዲስ ንጉሥ ተነሣ።

9፤ እርሱም ሕዝቡን። እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ሕዝብ ከእኛ ይልቅ በዝተዋል በርትተውማል፤

10፤ እንዳይበዙ፥ ሰልፍም በተነሳብን ጊዜ ጠላቶቻችንን አግዘው እንዳይወጉን ከምድሪቱም እንዳይወጡ፥ ኑ እንጠበብባቸው አለ።

11፤ በብርቱ ሥራም ያስጨንቁአቸው ዘንድ ግብር አስገባሪዎችን ሾመባቸው፤ ለፈርዖንም ፊቶምንና ራምሴን ጽኑ ከተሞች አድርገው ሠሩ።

12፤ ነገር ግን እንዳስጨነቁአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፥ እጅግም ጸኑ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ተጸይፈዋቸው ነበር።

13፤ ግብፃውያንም የእስራኤልን ልጆች በመከራ ገዙአቸው።

14፤ በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ፥ በጡብም በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፥ ሕይወታቸውን ያስመርሩአቸው ነበር።

15፤ የግብፅም ንጉሥ አንዲቱ ሲፓራ ሁለተኛይቱም ፉሐ የሚባሉትን የዕብራውያንን አዋላጆች እንዲህ ብሎ ተናገረ።

16፤ እናንተ የዕብራውያንን ሴቶች ስታዋልዱ፥ ለመውለድ እንደደረሱ ባያችሁ ጊዜ፥ ወንድ ቢሆን ግደሉት፤ ሴት ብትሆን ግን በሕይወት ትኑር።

17፤ አዋላጆች ግን እግዚአብሔርን ፈሩ፥ የግብፅ ንጉሥም እንዳዘዛቸው አላደረጉም፥ ወንዶቹን ሕፃናትንም አዳኑአቸው።

18፤ የግብፅም ንጉሥ አዋላጆችን ጠርቶ። ለምን እንዲህ አደረጋችሁ? ወንዶቹን ሕፃናትንስ ለምን አዳናችሁ? አላቸው።

19፤ አዋላጆቹም ፈርዖንን። የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብፅ ሴቶች ስላልሆኑ፤ እነርሱ ጠንካሮች ናቸውና አዋላጆች ሳይገቡ ስለሚወልዱ ነው አሉት።

20፤ እግዚአብሔርም ለአዋላጆች መልካም አደረገላቸው፤ ሕዝቡም በዛ፥ እጅግም ጸና።

21፤ እንዲህም ሆነ፤ አዋላጆች እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ ቤቶችን አደረገላቸው።

22፤ ፈርዖንም። የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ ወንዝ ጣሉት፥ ሴትን ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት አድኑአት ብሎ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ።