መጽሐፈ መክብብ 1

1፤ በኢየሩሳሌም የነገሠ የሰባኪው የዳዊት ልጅ ቃል።

2፤ ሰባኪው። ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል።

3፤ ከፀሐይ በታች በሚደክምበት ድካም ሁሉ የሰው ትርፉ ምንድር ነው?

4፤ ትውልድ ይሄዳል፥ ትውልድም ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ነው።

5፤ ፀሐይ ትወጣለች፥ ፀሐይም ትገባለች፥ ወደምትወጣበትም ስፍራ ትቸኵላለች።

6፤ ነፋስ ወደ ደቡብ ይሄዳል፥ ወደ ሰሜንም ይዞራል፤ ዘወትር በዙረቱ ይዞራል፥ ነፋስም በዙረቱ ደግሞ ይመለሳል።

7፤ ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፥ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደ ገና ወደዚያ ይመለሳሉ።

8፤ ነገር ሁሉ ያደክማል ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፤ ዓይን ከማየት አይጠግብም፥ ጆሮም ከመስማት አይሞላም።

9፤ የሆነው ነገር እርሱ የሚሆን ነው፥ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፤ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም።

10፤ ማንም። እነሆ፥ ይህ ነገር አዲስ ነው ይል ዘንድ ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተደርጎአል።

11፤ ለፊተኞቹ ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፤ ከኋለኞቹም ነገሮች ከእነርሱ በኋላ በሚነሡት ሰዎች ዘንድ መታሰቢያ አይገኝላቸውም።

12፤ እኔ ሰባኪው በእስራኤል ላይ በኢየሩሳሌም ንጉሥ ነበርሁ።

13፤ ከሰማይም በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ እፈልግና እመረምር ዘንድ ልቤን አተጋሁ፤ እግዚአብሔር ይደክሙባት ዘንድ ይህችን ለሰው ልጆች የሰጠ ክፉ ጥረት ናት።

14፤ ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።

15፤ ጠማማ ይቀና ዘንድ አይችልም፤ ጐደሎም ይቈጠር ዘንድ አይችልም።

16፤ እኔ በልቤ። እነሆ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ላይ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ጥበብን አብዝቼ ጨመርሁ፤ ልቤም ብዙ ጥበብንና እውቀትን ተመለከተ ብዬ ተናገርሁ።

17፤ ጥበብንና ዕብደትን ሞኝነትንም አውቅ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፤ ይህም ደግሞ ነፋስን እንደ መከተል እንደ ሆነ አስተዋልሁ።

18፤ በጥበብ መብዛት ትካዜ ይበዛልና፤ እውቀትንም የሚጨምር ኀዘንን ይጨምራልና።