ትንቢተ ሚክያስ 1

1፤ በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታምና በአካዝ በሕዝቅያስም ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው፥ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው፥ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።

2፤ እናንተ አሕዛብ ሁሉ፥ ስሙ፤ ምድርም ሙላዋም ታድምጥ፤ ጌታ እግዚአብሔርም፥ እርሱም በቅዱስ መቅደሱ የሆነ ጌታ፥ ይመስክርባችሁ።

3፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፥ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይረግጣል።

4፤ ተራሮችም በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፥ በገደልም ወርዶ እንደሚፈስስ ውኃ፥ በበታቹ ይቀልጣሉ፥ ሸለቆችም ይሰነጠቃሉ።

5፤ ይህ ሁሉ ስለ ያዕቆብ በደልና ስለ እስራኤል ቤት ኃጢአት ነው። የያዕቆብም በደል ምንድር ነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኮረብታው መስገጃ ምንድር ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን?

6፤ ስለዚህ ሰማርያን በሜዳ እንደሚገኝ የድንጋይ ክምር፥ ወይን እንደሚተከልበትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤ ድንጋዮችዋንም ወደ ሸለቆ እወረውራለሁ፥ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ።

7፤ የተቀረጹትም ምስሎችዋ ይደቅቃሉ፥ በግልሙትና ያገኘችው ዋጋ ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፥ ጣዖታትዋንም ሁሉ አጠፋለሁ፤ በግልሙትና ዋጋ ሰበሰበቻቸው፥ ወደ ግልሙትናም ዋጋ ይመለሳሉና።

8፤ ስለዚህ ነገር ዋይ ብላ ታለቅሳለች፥ ባዶ እግርዋንና ዕራቁትዋን ሆና ትሄዳለች፤ እንደ ቀበሮ ታለቅሳለች፥ እንደ ሰጐንም ዋይ ትላለች፤

9፤ ቍስልዋ የማይፈወስ ነውና፤ እስከ ይሁዳም ደርሶአልና፥ ወደ ሕዝቤም በር ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦአልና።

10፤ በጌት ላይ አታውሩ፤ በአኮ ላይ እንባን አታድርጉ፤ በቤትዓፍራ በትቢያ ላይ ተንከባለሉ።

11፤ በሻፊር የምትቀመጪ ሆይ፥ በዕራቁትነትሽና በእፍረት እለፊ፤ በጸዓናን የምትቀመጠው አልወጣችም፤ የቤትኤጼል ልቅሶ ከእናንተ ዘንድ መኖሪያውን ይወስዳል።

12፤ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ እስከ ኢየሩሳሌም በር ድረስ ወርዶአልና በማሮት የምትቀመጠው በጎነትን ትጠባበቃለች።

13፤ በለኪሶ የምትቀመጪ ሆይ፥ ሰረገላውን ለፈረስ እሰሪ፤ እርስዋ ለጽዮን ሴት ልጅ የኃጢአት መጀመሪያ ነበረች፤ የእስራኤል በደል በአንቺ ዘንድ ተገኝቶአልና።

14፤ ስለዚህ ትሎት ለሞሬሼትጌት ትሰጪአለሽ፤ የአክዚብ ቤቶች ለእስራኤል ነገሥታት አታላይ ይሆናሉ።

15፤ በመሪሳ የምትቀመጪ ሆይ፥ ወራሽ አመጣብሻለሁ፤ የእስራኤል ክብር ወደ ዓዶላም ይመጣል።

16፤ ተማርከው ከአንቺ ዘንድ ወጥተዋልና ስለ ተድላሽ ልጆች ራስሽን ንጪ፥ ጠጕርሽንም ተቈረጪ፤ ቡሃነትሽንም እንደ ንስር አስፊ።