ኦሪት ዘኍልቍ 16

1፤ የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ ከሮቤልም ልጆች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ ላይ ተነሡ። ች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ

2፤ ከእስራኤልም ልጆች ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች ከእነርሱ ጋር ወሰዱ፤ ከጉባኤው የተመረጡ ዝናቸውም የተሰማ የማኅበሩ አለቆች ነበሩ።

3፤ በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው። ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ? አሉ።

4፤ ሙሴም በሰማ ጊዜ በግምባሩ ወደቀ፤

5፤ ለቆሬም ለወገኑም ሁሉ። ነገ እግዚአብሔር ለእርሱ የሚሆነውን፥ ቅዱስም የሚሆነውን ያስታውቃል፤ የመረጠውንም ሰው ወደ እርሱ ያቀርበዋል።

6፤ እንዲሁ አድርጉ፤ ቆሬና ወገንህ ሁሉ፥ ጥናዎቹን ውሰዱ፤

7፤ ነገም በእግዚአብሔር ፊት እሳት አድርጉባቸው፥ ዕጣንም ጨምሩባቸው፤ እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር የሚመርጠው እርሱ ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች ሆይ እጅግ አብዝታችኋል ብሎ ተናገራቸው።

8፤ ሙሴም ቆሬን አለው። እናንተ የሌዊ ልጆች፥ ስሙ፤

9፤ የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር የለያችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ትሠሩ ዘንድ፥ እንድታገለግሉአቸውም በማኅበሩ ፊት ትቆሙ ዘንድ ወደ እርሱ ያቀረባችሁ አይበቃችሁምን?

10፤ አንተን ከአንተም ጋር የሌዊን ልጆች ወንድሞችህን ሁሉ ወደ እርሱ አቅርቦአል፤ ክህነትንም ደግሞ ትፈልጋላችሁን?

11፤ ስለዚህም አንተና ወገንህ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ተሰብስባችኋል፤ በእርሱም ላይ ታጕረመርሙ ዘንድ አሮን ማን ነው?

12፤ ሙሴም የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን እንዲጠሩአቸው ላከ፤ እነርሱም። አንመጣም፤

13፤ በምድረ በዳ ትገድለን ዘንድ ወተትና ማር ከምታፈስሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህምን? ደግመህ በእኛ ላይ ራስህን አለቃ ታደርጋለህን?

14፤ ደግሞ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር አላገባኸንም፥ እርሻና ወይንም አላወረስኸንም፤ የእነዚህንስ ሰዎች ዓይኖቻቸውን ታወጣለህን? አንመጣም አሉ።

15፤ ሙሴም እጅግ ተቈጣ፥ እግዚአብሔርንም። ወደ ቍርባናቸው አትመልከት፤ እኔ ከእነርሱ አንድ አህያ ስንኳ አልወሰድሁም፥ ከእነርሱም አንድ ሰው አልበደልሁም አለው።

16፤ ሙሴም ቆሬን። ነገ አንተ፥ ወገንህም ሁሉ፥ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁኑ፤

17፤ ሁላችሁም ጥናዎቻችሁን ውሰዱ፥ ዕጣንም አድርጉባቸው፥ እያንዳንዳችሁም ጥናዎቻችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት አምጡ፥ ሁለት መቶ አምሳ ጥናዎች፤ አንተ ደግሞ አሮንም ጥናዎቻችሁን አምጡ አለው።

18፤ እያንዳንዱም ጥናውን ወሰደ፥ እሳትም አደረገበት፥ ዕጣንም ጨመረበት፥ ከሙሴና ከአሮንም ጋር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆመ።

19፤ ቆሬም ማኅበሩን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእነርሱ ላይ ሰበሰበ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለማኅበሩ ሁሉ ተገለጠ።

20፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።

21፤ ሁሉን በቅጽበት አጠፋቸው ዘንድ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ።

22፤ እነርሱም በግምባራቸው ወድቀው። አምላክ ሆይ፥ አንተ የሰው ሁሉ ነፍስ አምላክ፥ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራ አንተ በማኅበሩ ሁሉ ላይ ትቈጣለህን? አሉ።

23፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

24፤ ለማኅበሩ። ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ዙሪያ ፈቀቅ በሉ ብለህ ንገራቸው።

25፤ ሙሴም ተነሥቶ ወደ ዳታንና ወደ አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት።

26፤ ማኅበሩንም። እባካችሁ፥ ከእነዚህ ክፉዎች ድንኳን ፈቀቅ በሉ፤ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳትጠፉ ለእነርሱ የሆነውን ሁሉ አትንኩ ብሎ ተናገራቸው።

27፤ ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ከዙሪያውም ሁሉ ፈቀቅ አሉ፤ ዳታንና አቤሮንም ሴቶቻቸውም ልጆቻቸውም ሕፃናቶቻቸውም ወጥተው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ቆሙ።

28፤ ሙሴም አለ። ይህን ሥራ ሁሉ አደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከኝ እንጂ ከልቤ እንዳይደለ በዚህ ታውቃላችሁ።

29፤ እነዚህ ሰዎች ሰው እንደሚሞት ቢሞቱ፥ ወይም እንደ ሰው ሁሉ ቢቀሠፉ እግዚአብሔር አልላከኝም።

30፤ እግዚአብሔር ግን አዲስ ነገር ቢፈጥር፥ ምድርም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ለእነርሱም ያለውን ሁሉ ብትውጣቸው፥ በሕይወታቸውም ወደ ሲኦል ቢወርዱ፥ ያን ጊዜ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደ ናቁ ታውቃላችሁ።

31፤ እንዲህም ሆነ፤ ይህን ቃል ሁሉ መናገር በፈጸመ ጊዜ ከበታቻቸው ያለው መሬት ተሰነጠቀ፤

32፤ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ቤተ ሰቦቻቸውንም፥ ለቆሬም የነበሩትን ሰዎች ሁሉ፥ ዕቃዎቻቸውንም ሁሉ ዋጠቻቸው።

33፤ እነርሱም ለእነርሱም የነበሩ ሁሉ በሕይወታቸው ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም ተዘጋችባቸው፥ ከጉባኤውም መካከል ጠፉ።

34፤ በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ከጩኸታቸው የተነሣ። ምድሪቱ እንዳትውጠን ብለው በረሩ።

35፤ እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥታ ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላች።

36፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

37፤ ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር እንዲህ ብለህ ንገረው። ተቀድሰዋልና ጥናዎቹን ከተቃጠሉት ዘንድ ውሰድ፥ እሳቱንም ወደ ውጭ ጣለው፤

38፤ በኃጢአታቸው ሰውነታቸውን ያጠፉትን የእነዚያን ሰዎች ጥናዎች ጠፍጥፈህ ለመሠዊያ መለበጫ አድርጋቸው፤ በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋቸዋልና የተቀደሱ ናቸው፥ ለእስራኤልም ልጆች ምልክት ይሆናሉ።

39፤ ካህኑም አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች ያቀረቡአቸውን የናስ ጥናዎች ወስዶ ጠፍጥፎም ለመሠዊያው መለበጫ አደረጋቸው።

40፤ በቆሬና በወገኑ የደረሰው እንዳይደርስበት፥ ከአሮን ልጆች ያልሆነ ሌላ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ዕጣን ያጥን ዘንድ እንዳይቀርብ፥ እግዚአብሔር በሙሴ እንደ ተናገረው፥ ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ አደረጋቸው።

41፤ በነጋውም የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ። እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ።

42፤ እንዲህም ሆነ፤ ማኅበሩ በሙሴና በአሮን ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን አዩ፤ እነሆም፥ ደመናው ሸፈነው፥ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠ።

43፤ ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት መጡ።

44፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

45፤ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ፥ እኔም በቅጽበት አጠፋቸዋለሁ። በግምባራቸውም ወደቁ።

46፤ ሙሴም አሮንን። ጥናህን ውሰድ፥ ከመሠዊያውም ላይ እሳት አድርግበት፥ ዕጣንም ጨምርበት፥ ወደ ማኅበሩም ፈጥነህ ውሰደው አስተስርይላቸውም፤ ከእግዚአብሔር ፊት ቍጣ ወጥቶአልና መቅሠፍት ጀምሮአል አለው።

47፤ አሮንም ሙሴ እንደ ተናገረው ጥናውን ወስዶ ወደ ጉባኤው መካከል ሮጠ፤ እነሆም፥ መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፤ ዕጣንም ጨመረ፥ ለሕዝቡም አስተሰረየላቸው።

48፤ በሙታንና በሕያዋን መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ።

49፤ በቆሬም ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት አሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።

50፤ አሮንም ወደ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ።