ኦሪት ዘፍጥረት 22

1፤ ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ እንዲህም አለው። አብርሃም ሆይ። አብርሃምም። እነሆ፥ አለሁ አለ።

2፤ የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ።

3፤ አብርሃምም በማለዳ ተነሥቶ አህያውን ጫነ፥ ሁለቱንም ሎሌዎቹንና ልጁን ይስሕቅን ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ እንጨትንም ለመሥዋዕት ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ሄደ።

4፤ በሦስተኛውም ቀን አብርሃም ዓይኑን አነሣና ቦታውን ከሩቅ አየ።

5፤ አብርሃምም ሎሌዎቹን አላቸው። አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ሄደን እንሰግዳለን፥ ወደ እናንተም እንመለሳለን።

6፤ አብርሃምም የመሥዋዕቱን እንጨት አንሥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው፤ እርሱም እሳቱንና ቢላዋውን በእጁ ያዘ፥ ሁለቱም አብረው ሄዱ።

7፤ ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን ተናገረው። አባቴ ሆይ አለ። እርሱም። እነሆኝ፥ ልጄ አለው። እሳቱና እንጨቱ ይኸው አለ፤ የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት ነው? አለ።

8፤ አብርሃምም። ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለው፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ።

9፤ እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያውን ሠራ፥ እንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው በእንጨቱ ላይ አጋደመው።

10፤ አብርሃምም እጁን ዘረጋ፥ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ።

11፤ የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና። አብርሃም አብርሃም አለው፤

12፤ እርሱም። እነሆኝ አለ። እርሱም። በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ።

13፤ አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፥ በልጁም ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው።

14፤ አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ ይርኤ ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእግዚአብሔር ተራራ ይታያል ይባላል።

15፤ የእግዚአብሔር መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለተኛ ጊዜ ጠራው፥

16፤ እንዲህም አለው። እግዚአብሔር። በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና

17፤ በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፥ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤

18፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፥ ቃሌን ሰምተሃልና።

19፤ አብርሃምም ወደ ብላቴኖቹ ተመለሰ፥ ተነሥተውም ወደ ቤርሳቤህ አብረው ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ተቀመጠ።

20፤ ይህም ከሆነ በኋልላ ለአብርሃም እንዲህ ተብሎ ተነገረ። እነሆ፥ ሚልካ ደግሞ ለወንድምህ ለናኮር ልጆችን ወለደች፤

21፤ እነርሱም በኵሩ ዑፅ፥ ወንድሙ ቡዝ፥ የአራም አባት ቀሙኤል፥

22፤ ኮዛት፥ ሐዞ፥ ፊልዳሥ፥ የድላፍ፥ ባቱኤል ናቸው።

23፤ ባቱኤልም ርብቃን ወለደ፤ እነዚህን ስምንቱን ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር ወለደች።

24፤ ሬሕማ የሚሉአት ቁባቱ ደግሞ ጥባህን፥ ገአምን፥ ተሐሸን፥ ሞክሳን ወለደች። a