0:00

መዝሙረ ዳዊት 138

1 የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ የአፌን ነገር ሰምተኸኛልና፤ በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ።

2 ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ምሕረትህና ስለ እውነትህ ስምህንም አመሰግናለሁ፥ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሃልና።

3 በጠራሁህ ቀን በፍጥነት አድምጠኝ፤ ነፍሴን በኃይልህ በብዙ አጸናሃት።

4 አቤቱ፥ የምድር ነገሥታት ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ የአፍህን ቃል ሁሉ ሰምተዋልና።

5 በእግዚአብሔርም መንገድ ይዘምራሉ፤ የእግዚአብሔር ክብር ታላቅ ነውና።

6 እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና፥ ወደ ችግረኞችም ይመለከታልና፤ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል።

7 በመከራ መካከል እንኳ ብሄድ፥ አንተ ሕያው ታደርገኛለህ፤ በጠላቶቼ ቍጣ ላይ እጆቼን ትዘረጋለህ፥ ቀኝህም ታድነኛለች።

8 እግዚአብሔር ብድራትን ይመልስልኛል፤ አቤቱ፥ ምሕረትህ ለዘላለም ነው፤ አቤቱ፥ የእጅህን ሥራ ቸል አትበል።