0:00

መዝሙረ ዳዊት 14

1 ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

ሰነፍ በልቡ። አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጐስቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም።

2 የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ።

3 ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም።

4 ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፥ በምላሳቸው ሸነገሉ፤

5 ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ፤ አፋቸው መርገምንና መራራን ተሞልቶአል፤

6 ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፤ ጥፋትና ጕስቍልና በመንገዳቸው አለ፥ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና፤ እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም።

7 ሕዝቤን እንደ እንጀራ የሚበሉ ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ በውኑ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም።

[8] በዚያ በታላቅ ፍርሃት እጅግ ፈሩ፥ እግዚአብሔር በጻድቃን ትውልድ ዘንድ ነውና።

[9] የድሆችን ምክር አሳፈራችሁ፥ እግዚአብሔር ግን ተስፋቸው ነው።

[10] ከጽዮን መድኃኒትን ለእስራኤል ማን ይሰጣል? እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ ያዕቆብ ደስ ይለዋል፥ እስራኤልም ሐሤት ያደርጋል።