0:00

መዝሙረ ዳዊት 99

1 የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ነገሠ፥ አሕዛብ ይደንግጡ፤ በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ፥ ምድር ትናወጥ።

2 እግዚአብሔር በጽዮን ታላቅ ነው፤ እርሱም በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ አለ።

3 ግሩምና ቅዱስ ነውና ሁሉ ታላቅ ስምህን ያመስግኑ።

4 የንጉሥ ክብር ፍርድን ይወድዳል፤ አንተ ቅንነትን አጸናህ፥ ለያዕቆብ ፍርድንና ጽድቅን አንተ አደረግህ።

5 አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ ቅዱስ ነውና ወደ እግሩ መረገጫ ስገዱ።

6 ሙሴና አሮን በካህናቱ ዘንድ፥ ሳሙኤልም ስሙን በሚጠሩት ዘንድ ናቸው። እግዚአብሔርን ጠሩት፥ እርሱም መለሰላቸው።

7 በደመና ዓምድም ተናገራቸው፤ ምስክሩንና የሰጣቸውን ትእዛዝ ጠበቁ።

8 አቤቱ አምላክችን ሆይ፥ አንተ ሰማሃቸው፤ አቤቱ፥ አንተ ማርሃቸው፥ ሥራቸውን ሁሉ ግን ተበቀልሃቸው።

9 አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ በቅዱስ ተራራውም ስገዱ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና።